ለአፋርነታችን ያለን ምልከታ ለዘረኝነት ያለን ጥላቻ ጋር እንዴት ይታረቅ ❓

ለአፋርነታችን ያለን ምልከታ ለዘረኝነት ያለን ጥላቻ ጋር እንዴት ይታረቅ ❓

ግንቦት 10/09/2012  ዓ.ም
✍️ ሀሰን ዋሬ ነስሪ
በዘረኝነትና በጥቅም ፈለገ ያበደ ትውልድ
የአፋር ብሄር ይደራጁ አይደራጁ’  በፈለገው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ቢገዙ: ከየትኛውም ጎሳና ዘር ይምጡ ከየትም ይሁኑ የት:አፋርነት ስሜት  እስካላቸው ደህንነታቸው እንዲጠበቅና ፍትህን ይሻሉ ይግባቸዋልም:: ሌላው ከዚህ የዘለለው ጉዳይ አፋርን ወደ ከፍታዋ ለማውጣት በሚደረግ ትግል ውስጥ የምናራምደው ፍላጎት መገለጫ ቢሆን እንጂ ለገዛ ጎሳችን ስንል ዘር ቆጥረን የምንታገልለት ወይም ሌሎች ላይ የምንጭነው እሴታችን አይደለም::

ምን አይነት አስተዳደራዊ ወሰን እና የፖለቲካ ትርክት ይኑረን እንዴትስ እንመራ? የሚለው ጥያቄ የላቀና ዘለቄታዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እኩል ተጠቃሚነት ሲባል የሚነሳ ሲሆን በሰላም ወጥቶ ለመግባትና በሕይወት ለመቆየት እንዲሁም ግድ ለሚሉን መሰረታዊ ፍላጎቶች መሟላት ለሚደረግ ሩጫና ከአንዲት ሉዓላዊ ክልላችን ለሚጠበቅ ተራ የጎሳ ጥቅማ ጥቅም መከበር ግን ይህን ያህል ፈታኝ የቤት ሥራ ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ:: ለመሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ታታሪነታችን አፋሪነታችንና አብሮነታችን እንዲሁም ለእስካሁን ያኖረንን አኩሪ የባህል እሴትንና እምነትን መጎናጸፍ በቂ ነው::

ከዚህ ውጭ ግን ያውም ለሺህ ዓመታት በአብሮነት ተከባብረው ስለመኖራቸው ስለተመሰከረላቸውና ለውጭ ጠላት አይበገሬ ነን ለሚሉ ህዝቦች አሁን የምናየውን አይነት የርስ በርስ መጠቃቃትና መገፋፋት ሁኔታ መበራከት ምንጩ ዘረኝነት ነው:: ወረድ ሲልም ለግል ጥቅሙ የጎሳ እና ጎሳ ጥቃትና ግጭት ለመድራስ የምሮጠው ትርፉ ሞራላዊ ዝቅጠትና እሱን የሚመራው/የሚነዳው መዋቅር መላሸቅ የሚያሳይ እንጂ ሌላ አይደለም::

ይሄው ከጊዜ ወደ ጊዜ መርዙን እየረጨ እርስ በርስ ልያባላን ያለው ዘረኝነት እየረጨ ያለህ በአፋሪነት የተደራጁና በገዛ ክልሉ በአፋር አርብቶ አደሮች ለይ ወራራ እያደረገ ያለው የሶማሌላንድ የኢትዮጵያ ሶማሌ የጅቡቲ መንግስት ሰረጎገቦችን ለመመከት የያዙት አቋም ሊመሩት ከሚፈልጉት ሕዝብ ፍላጎት የሚጣረስ እና ከማህበረሰቡ የወረደ ተልዕኮ እንዶኖራቸውና መርህ አልባ ያደረገ መሆኑን ታዝቢያለሁ:: የማህበራዊ ሚዲያዎቻችን የሚጠቀሙ ወጣቶች ሕብረ አፋራዊነትን ከማቀንቀን (“የትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን ህልም ከመፍታት) ይልቅ ወደ አንድ ጎሳና ለጥቂት የጥቅም -ተኮር ለሆነው ቡድን/የፖለቲካ አቋም ያደሉ አልያም አፍቅሮተ ነዋይ የተጠናወታቸው እንጂ ለህዝብ ወገንተኝነታቸውን ማሳያየት የተሳናቸው ወደ ነፈሰበት የሚነፍሱና ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ በዘላቂነት በትውልድ ላይ መፍጠር ያልቻሉ የሆድ አምላክዎች እየተበራከቱ በአፋር ህዝብ ስም በመነገድ በአንድ ጎሳና ቡድን ጥቅም ለማስከበር ከነፍስ አባቶቻቸው የተሰጣቸውን የአንድ ጎሳ እና ቡድን ጩሄት ሰለባዎቹ እንደሆኑ አሉ::

በርካታ ምሁራንና አክትቪስቶችም ክልላዊ እሴትን ሊጨምሩ ይችላሉ የሚባሉ ሃሳቦች ያመነጫሉ ተብሎ ሲጠበቅ “ጭር ሲል አልወድም” አይነት አጀንዳዎችን ሲያራምዱና መጣሁበት ከሚሉት የተከበረው የአፋር ህዝብ ስም እየተዋሱ ጎሳና ቡድን ለግለሰቦች  ከዘረኝነት የተጣበቁ አስተያተቶችን በማንሳት ቅቡልነትን ለማግኘት ሲሯሯጡ ይስተዋላል:: ክልላችን እስካሁን ጸንታ የቆመችበት የባህልና የታሪክ እሴቶችን ነቅሶ ከማውጣትና የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ከማድረግ ይልቅ አብዛኛው ሊባል በሚባል ደረጃ የጎሳና ዘር የጥቂት ቡዶን ውላጅ ሃሳቦችን በየማህበራዊ ሚድያዎች እየዘራ ይገኛል:: ትናንትናና ዛሬ ላይ ቆም ብልን እነዚሁ ምሁራንና አክቲቪስቶች ያራምዱት ስለ ነበረው ትርክት ስንመረምር የምናገኛቸው በተለያየ ጫፍ ቆመው ህዝቡን መሃል ላይ ማግደው እሳት ሲሞቁ ነው::

የእኔ ልቅደደምና እኔ ብቻ ስሙኝ አባዜ/ጎሰኝነት ከምንም በላይ ደግሞ ከዚህ በኃላ ለአፋራዊነት ከሚከፈል ዋጋ ይልቅ ለወጡበት ጎሳ /ቡድን  እና የዞነዊ አስተዳደራዊ መዋቅር ወይም ሌላ ግልጽ ያልሆነ ጥግ ይዘው ለቆሙለት አላማ የላቀ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁነት እያሳዩ ያሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን እታዘባለው::

ሌላው ቀርቶ በትውልድ/በመኖሪያ አካባቢያችን ያለውን ስር የሰደደ ድህነት ለመቀነስና ማህበረሰባችንን በልዩ ሁኔታ ለመጥቀም ሲባል የሚደራጁ የልማትና መረዳጃ ማህበራትም እንዲሁ የዚያን አካባቢ ቀዳማይ ብሔር ስም ካለተለጠፈበት ለእርዳታ እጆቻቸውን ላለመዘርጋት ሲዳዱ ይታያል:: “እኔ የጎሳ ፖለቲካና አደረጃጀት አይመቸኝም::” ብሎ ሲያበቃ በል እንግዲያው የሶማ አሸባሪዎች የእየተጠቁ ያሉትን የአፋር አርብቶ አደሮች በአቅምህ ለግስ አልያም ደግሞ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል አዋጣ ሲባል መግቢያ ይጠፋዋል ።እንኳን ለክልል ለሀገር እንኳን እንድትለማ አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ የተባሉና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ያጠናክራሉ ተብለው የሚቀረጹ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ አይደለም የአርብቶ አደር ህዝባችን በሀሳብ በማቀራረብ የራሳቸውን ሚና ከመጨወት አንድ የሆነውን የአፋር ህዝብ የምቃርንበት ሁኔታ እንኳ ከዚህ የጎሰኝነት ደዌ መመታታችን ሁነኛ ማሳያ እየሆነ መጥቷል ::

የሆነው ሆኖ አብዛኞቻችን ዘረኝነትን የምንጠየፍ መሆናችንን ከመደስኮር በዘለለ የጎሳም ሆነ የቡድን -ተኮር አቋም ስናራምድ ለሕዝባችን በተለይም ነገ ላይ እንድናያት ለምንሻት የበለፀገችና በሦስትም መአዛን አንድነቱ የተጠናከረ አፋርን ለመመስረት ያለውን ፋይዳ በተጨባጭ በማስረዳት ቢሆን መልካም ነው:: ጎሳና የአስተዳደር መዋቅር በማንም ምርጫ ለማንም የተሰጠ አይደለም:: አንዱ ካንዱ የማያንስም የማይበልጥም% በማንም ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ህልውና የሌለውና ሰው በመሆናችንን ሲቀጥል የትውልድ አካባቢያችንን ተከትሎ የምንጎናፀፈው እንጂ ማንንም አሸማቀን እኛ የምንከብርበት አይደለም:: ጎሳችን የአፋራዊነታችን መገለጫ ከሆነው ቀለም ውስጥ አንዱ መለያችን ቢሆን እንጂ በራሱ ህልውናችን ሊሆን አይችልም ።

ለሚገጥሙን ማናቸውም ችግሮች የጎሳና ዘር ካርታ እየመዘዙ መፍትሄ ለማበጀት ከማሰብ ይልቅ በጥንቃቄ ለተለዩ ችግሮቻችን ያ ጎሳ/ጎሰኝነት /ብሄረሰብና ሕዝብ ያለፈበት የታሪክ: የባህልና ሌሎች ገንቢ እሴቶችን በመመንዘር የላቀ አገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው በማድረግ መንቀሳቀስ እና የተጣባንን የዘርኝነት ደዌ አሽቀንጥረን መጣል ብንችል ምን ይለናል?

አፋራዊ ርዕይ እና ስሜት የሌለው የትኛውም አካል የብሔርና ጎሳዊ  ጉዳዮችን ነጣጥሎ ለማየት አይቻለውም:: ‘እኔነት’ ከ ‘እኛነት’ የተሻለ ፋይዳ የለውም:: ሲጀመር ማንም እየተነሳ ጎሳየ ተነካ እያለ በማላዘን የየዋሁን ሕዝቤን እረፍት ነስቶ ግድ ያልሆነበትን ጥያቄ አንስቶ መልስ አፈላላጊ መስሎ የሚቀርብበት ጊዜም ሊበቃ ይገባል:: ሁሉም ጊዜና ሁኔታ በፈቀደ መጠን ለዚች ለአንድ አፋርነት ዋጋ በከፈለባትና ለዛሬ ባበቃት አገር ላይ በዘርና ጎሳ ስም አንዱ አንዱን አጥቅቶ ወደ የትም ሊሸሸግ አይችልም  አብረን በዚህችው ክልል ጥላ ስር እስከኖርን ድረስ ለትውልድ የምናወርሰው ሌላ ተጨማሪ ጠባሳ ከየትኛውም ወገን እንዳይነሳ የታሪክ ተወቃሽም እንዳንሆን መትጋቱ ነው መልካሙ መንገድ::

ከምን በላይ አሁን ዘመኑ የመስከን እንጂ በዘር ደዌ የተመታ ስብእናና ብእር ይዘው እኔ… እኔ እያሉ እራሳቸውን እያስቀደሙ ሕዝቡን ለጥፋት የሚማግዱበት አይደለም:: አያንዳንዱ ያለውን አንድ የአፋር እሴት አሟጦ ለአገር የሚተርፍ አንዳች ነገር ማመጣት የሚያስችሉ አማራጮችን ከማስፋት ውጭ በጠበበው መንገድ ካልሄድኩ ብሎ ማለት አያዋጣም  ይህን ማድረግ ባንችል እንኳን ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርባት: ሕግና ስርዓት የሰፈነባት ክልል እንድትኖረን ማድረግ እየተቻለ ማንም ያሻውን ወንጀልና ወከባ እየፈፀመ ጎሰኝነት ስር የሚሸጎጥበት ሁኔታ ማብቃት አለበት:: ማናችንም የህይወት ውጣ ውረድ እና የየዕለት ኑሮአችንን ለማሸነፍ በምናደርገው ትግል ከየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ጋር ያለን መስተጋብር ጤናማነት እንጂ የታመመና የጎሳ ትርክት ያሰከረው ማንነት አይደለም አሸናፊ የሚያደርገን::

ስለ ዘርና ማንነት እንዲሁም አስተዳደራዊ ጥያቄዎች በአብዛኛው የፖለቲካ ምህዋሩን የሚዘውሩ አካላት የሚያነሱት በዚህ ሂደትም ወጣቱን ለዚሁ አላማቸው የምያሰልፉበት(ተሳክቶላቸው እንደሆን እኛንም በቅጡ የሚያስተዳድሩበት ያህል ካልሆነ ግን የቀጥቅቱ ቅጡ ትርክት የሚነዙበት) እንጂ ሰፊው ህዝብማ ከሰላሙ’ የአብሮነት ሕይወቱና የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ከሚያደርገው ሩጫ በልጦበት የሚያነሳው ይህን ያህል የጎላ ጥያቄ ያለም አይመስለኝም:: ቢሆንም እንኳን በሰከነና ሕግና ስርዓትን ተከትሎ እንዲፈፀም ይተጋል እንጂ እንዲህ በታሪክ ከሚወቀስበት ቅሌት ውስጥ ለመግባት አይዳዳም:: እናም የድህነትን ቀንበር ከጫንቃው ላይ ያላነሳ ሕዝብ ሌላ ሸክም ሆነን ባንጫነዉ መልካም ነው::

በየአከባቢያችን በገዛ መሬቱ በወራሪዎች ለሞትና እንግልት አርብቶ አደሩ ህዝባችንን የምያዳርገውና ዛሬ ከግዛቴ ውጣ እያለን ወገናችንን ሰላም የሚያሰጠው በየ አቅጠጫው ተበራክቶ እያለ ሁላ መነሻችንን ካለማወቅ የአለምን አይደለም የራሳችንን የነገዋን አዳራችንን ሁኔታ መገመት ካለመቻል የምንፈጥረው ሁኔታ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል:: ዘረኛና ራስ ወዳድ ሰዎች ሁሌም የሚሸጎጡበት ጥግ በጨለማ የተዋጠና በውጤቱም መጠፋፋት የሆነ ነው:: የትኛውንም ጎሳ /ዘረ ማብቃትና የላቀ ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው በሌላው ላይ መከራና ግፍ በመጫን ሳይሆን ስልጡንና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል እና ፍትሃዊ አስተዳደርን በማስፈን እንዲሁም ማህበረሰባችን ሲገዛበት የኖረውን የሃይማኖትና ባህል አኩሪ እሴቶችን ጥቅም ላይ በማዋልና ለሞራላዊ ልዕልና በመገዛት ነው:: ከዚህ ውጪ እራስን በራስ የማስተዳደርም ይሁን የማንነት መብት ተከብሮልን ልዩነት የለለው አንድ አፋር ህዝባችን ለአመታት አብሮት የኖረውን እና የቤተሰቡን ሕይወት ለማሻሻል የትውልድ ቀዬውን ጥሎ እንስሳትን ተከትሎ እየተሰደደ ያለውን ምስኪን ወገኑን ለመግፋት የሚደረገው ጬሄት  በህግም ሆነ በአፋር ባህል የተከለከለ እና በሃያ አንደኛው መቶ አመት አስተሳሰብ የማይወክል የወረደ አስተሳሰብ መሆኑን እና ከስልጠን ጥመኝነት እና ከጥቅም አሳደጅነት ያልዘለለ አንድ ቤተሰብ የሆነውን አፋር ከማፍረስ ጋር ይያያዛል? በጎሳ ስም እየነገዱ ህዝቡ ያልበላውን ልከክልህ እያሉ የተጣባቸውን የዘረኝነትና ግለኝነት ባህሪያቸውን ለማስረፅና የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ድክድክ ሲሉ የሚታዩ በዙዎች ናቸው::

ዘረኝነት አለምን የምናይበት መነጽር ተገልብጦ የራሳችንን ምስል የምንፈጥርበት እሱንም አልተገለበጠም የኔው ነው ብቸኛና ትክክለኛ ምስል ብሎ እንደመዘላበድ አይነት እብደት የሚታይበት ማንነት ነው በተሳከረ እይታ የጠራ አፋራዊ ምስል መመዕልከት አይቻልም:: አይደለም በጎሳና አፋርነታችንን ላይ  ላይ ያለን እይታ እራሱ ልክ አለው:: የጠራው እይታ ከተንሸዋረረው መለየት የምንችለው ስክነት’ እውቀት’ ብስለት’ ልምድና ሚዛናዊ አመለካከቶችን ማዳበር ስንችል ነው::

በኔ እይታ የቱንም ያህል የአፋር ፍቅር ቢኖረን የቱንም ያህል የኛ የምንለው አኩሪ እሴት እንደ አፋር ማህረሰብ ብናተርፍ እንኳ በኢትዮጵያ ምትክ የሌለውና ከሁሉም ገዝፈን የምንወጣበት ያን ያህል ማንነት እንድኖረን አንድ መሆን መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል :: አባይን ያላየ ምንጭ ያመሰግናል እንዲሉ ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ጀምሮ በርካታ አስገራሚ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ እሴቶች ምድርን ሞልተዋት ሳለ የታሪክና የርስቱ ባለቤቶች እኛ ብቻ የሆንን እያለን ርሃብና ስር የሰደደው ድህነት አንዱ ምንጭ ይሄን መሰል ልክ የሌለው አመለከታችን መሆኑ እሙን ነው::

ካንዱ ጎሳ  የበለጠ ለመጠቀም ከሚከጅለውና የሚገባውን ክልላዊ ጥቅም ከቀደሙ ጊዚያቶች በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ከሚታትረው ማህበበረሰብ ክፍል መካከል ያሉ የትግል አካሄዶች የጎሳ ዳዋ ከዋጠው አካልና ለፍትህ ከቆመው መካከል ሰፊ ያስተሳስብ ልዩነት አለ:: በአንድ የጋራ በምንላት ክልል ውስጥ ሆነን የአንድን ጎሳ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል የምናስበረግገው/የምንነሳበት ሌላ ወገን መኖር አለበት ብሎ የሚያምን አካል ካለ እሱ ዘረኛና በአስተሳሰብም የአፋር ማህበረሰብ ጥላ ስር መጠለል የማይገባው ስለመሆኑ ተገልፆ ልናወግዘው ይገባል:: ከከፋ የዘረኝነት ደዌ እንዲጠበቅና በአፋር ብሄረሳበዊነቱ ኮርቶ ለሌላውም ኩራት እንዲሆን የአፋራዊነት ጸበል ማጥመቅ የግድ ይላል::

Leave a comment